ጳጉሜ 3/2014 (ዋልታ) ዓለም ዐቀፉ የቴሌኮም ኅብረት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ ኢትዮጵያን የምትሰራቸውን ስራዎች እንዲደግፍ ተጠየቀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒኤችዲ) ለዓለም ዐቀፉ የቴሌኮም ኅብረት ዋና ፀኃፊነት የሚወዳደሩት የድርጅቱ የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ቢሮ ዳይሬክተር ዶሪን ቦግዳን -ማርቲን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ሚኒስትሩ እንደ ኅብረት ያሉ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ የምትሰራቸውን ስራዎች በቴክኒክ እና በሌሎችም ጉዳዮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ዳይሬክተር ዶሪን ቦግዳን በበኩላቸው የዋና ፀኃፊነቱን ቦታ ለመያዝ የኢትዮጵያን ድጋፍ ጠይቀዋል።
ኅብረቱ ጠቅላላ ጉባኤ ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም በሩማኒያ ቡካሬስት የሚካሂድ ሲሆን በዚሁ ጉባኤ ላይ ኅብረቱን ለሚቀጥለው 4 አመታት የሚመሩትን ከፍተኛ ኃላፊዎችን ይመርጣል።
በአሜሪካ አቅራቢነት ከሚወዳደሩት ሚስ ዶሪን ቦግዳን በተጨማሪ ሩሲያዊው ሚር ራሺድ ኢስማኤሎቭ ለድርጅቱ ዋና ጸኃፊነት የሚወዳደሩ እንደሚሆን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
ጠቅላላ ጉባኤው የኅብረቱ ከፍተኛው የስልጣን አካል ሲሆን በየ4 አመቱ ድርጅቱን የሚመሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚመርጡበት እና የኅብረቱ አባል የሆኑ 193 አገራት በመራጭነት የሚሳተፉበት ነው።