የኢድ-አል ፈጥር በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን የሀረር ነዋሪዎች ገለጹ

የካቲት 29/2014 (ዋልታ) የኢድ-አል ፈጥር በዓልን እንዲሁም በክልሉ በልዩ ሁኔታ የሚከበረውን የሸዋል-ኢድ በዓልን ለማክበር ወደ ሀረር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
መጪውን የኢድ-አል ፈጥርና ሸዋል-ኢድ በአላትን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እንደተደረገና በተለይም ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው የኢድ-አል ፈጥርና ሸዋል-ኢድ በአላትን ለማክበር ከተለያዩ የዓለም ሀገራትና የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በሚከናወኑ ተግባራት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብም ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ቤቱን ክፍት አድርጎ መጠበቅ እና በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባው መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት አካባቢን የማስዋብና የማጽዳት ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።