የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ የምዕራብ አየር ምድብን ጎበኙ

የምዕራብ አየር ምድብ  የሕወሐት ጁንታን ሴራ ለማክሸፍ በተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ  ለፈጸመው ተጋድሎ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ምስጋና አቅርበዋል።

ሜጀር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፣ በምድቡ ጠቅላይ መምሪያ በመገኘት የምድቡ ሰራዊት ጁንታው ያሴረውን ሀገርን የማተራመስ እቅድ ለማክሸፍ አመራሩ በጥበብ፣ አባላቱም በጀግንነት ውሎ ለፈፀማችሁት አኩሪ ገድል ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።

“የሀገር መከታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ሰው በላው ቡድን የራሱን ጓድ ከኋላው ሆኖ በመውጋቱ የገጠማችሁን ልብ የሚሰብር ሀዘን ችላችሁ፣ የምድቡ አመራርና አባላት ቅንጅት በመፍጠር በሀገራዊ ሞራልና ስሜት የሕዝብ ልጅ መሆናችሁን በተግባር አስመስክራችኋል” ብለዋል።

በቀጣይም አየር ኃይሉ የቴክኖሎጂ አቅሙን እና ክህሎቱን በማሳደግ ከማንኛውም የፓለቲካ ፓርቲ አስተሳሰብ  ፍፁም ነፃ በመሆን ፣ የሪፎርም አደረጃጀቱን ይበልጥ በማጠናከር ልክ እንደስካሁኑ የሀገር መከታነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ዋና አዛዡ  በምድቡ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የግዳጅ ዝግጁነቱን መጎብኘታቸውን ከኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ  ያመለክታል።