የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አንደኛው የፓርላማ የምርምር ኮንፈረንስ ተጀመረ

 

                                             የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛው የፓርላማ የምርምር ኮንፈረንስ ̎

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2013 (ዋልታ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛው የፓርላማ የምርምር ኮንፈረንስ ̎ፓርላማ፣ ዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብቶች ̎በሚል ርዕስ በመንግስታቱ ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ÷በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ምክር ቤቶች የዴሞክራሲ ስርዓት መገንቢያ መድረክና መሳሪያ ሆነው እንደሚያገለግሉ ገልፀዋል፡፡

በዚህ ዘመን በተለይ እያደጉ ባሉና በሽግግር ላይ ባሉ ሀገራት ምክር ቤቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር የሚያደርጉት የሰመረ ግንኙነት የሀገራቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በመፍታትና ሀገራቱን በማሳደግ በኩል አይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ነው የገለጹት ፡፡

ኢትዮጵያ የማደግ እምቅ አቅም እና ተስፋ ያላት ናት ያሉት አፈ-ጉባኤው÷ ይህን አቅም ወደ ተግባር ለመቀየርና ተስፋችንን እውን ለማድረግ ደግሞ ጥናትና ምርምር ወሳኝ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለው ባመኑባቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ይከራከራሉ፣ ህግ ያወጣሉ፣ መንግሰትን ይቆጣጠራሉ ብለዋል፡፡

በዚህም በምክር ቤቱ የሚደረጉ ክርክሮች እንዲሁም የሚወጡ ህጎች ደግሞ በጥናት የተለዩ፣ በቂ ማስረጃ ያላቸውና አመክኖአዊ ምክረሃሰብ ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ ተቀባይነት ያላቸውና ለታሰበላቸው ኣላማ ሊውሉ የሚችሉ ውሳኔዎችና ህጎች የማውጣት እድላቸው ይሰፋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚያም ባለፈ ህግ ፈጻሚው በተነጻጻሪነት የተሻለ የመረጃ እና የእውቀት ምንጮች ያሉት በመሆኑ ምክር ቤቶች ህግ አውጪውን በሚቆጣጠሩበት ወቅት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የመረጃ እጥረት መሙላት የሚያስችል አሰራር መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህን በመረዳት የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህገ መንግሰቱ የተሰጡትን ተልእኮዎች ሲወጣ የሚያከናውናቸው ተግባራት በመረጃ፣ በእውቀት እና በተቀመረ ልምድ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የዛሬው መድረክም የፓርላሜንታዊ የምርምር መረብ መጠናከር ምክር ቤቱ እያካሄደ ለሚገኘው የለውጥ አካሄድ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥና ፓርላማውም በጥናትና ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ በተለይም በሕግ አወጣጥ፤ በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የውክልና ተግባራትን በተገቢው ሁኔታ ለማገዝ የሚረዳ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ኔትወርኩ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የምርምር ተቋማትን፣ ሃሳብ አመንጪ ተቋማትን(ቲንክ-ታንክ)፣ የሲቪል ማኅበረሰቡንና የሙያ ማህበራትን ችግር ፈቺ የሆኑ የምርመር ተግባራትን በማካሄድ የሚጠበቅባቸውን ለብሄራዊ ልማት አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችሉ ለማስቻል የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ የምርምር መረብ ራሱ ከሚያበረክታቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ባሻገር የምክር ቤቱን የጥናትና ምርምር አቅም በመገንባትም ወሳኝ ሚና እንዲጫወት እንጠብቃለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኮንፈረንሱ የሚቀርቡት የጥናት ጭብጦችም ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተመረጡ በመሆናቸው ለታሰበው አላማ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

እንዲህ አይነቱ የምርምር ኮንፈረንስ በመደበኛነት በየአመቱ የሚከናወኑ ሲሆን ኮንፈረንሱ የሁለት ቀናት ቆይታ እንደሚኖረው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።