ነሐሴ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢፌዴሪ የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መገባቱን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁን ተከትሎ ፖሊሲውን ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚረዱ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጿል፡፡
ከነዚህ ሥራዎች መካከል አንዱ የሸግግር ፍትሕ ፖሊሲውን አፈፃፀም፣ ክትትልና ድጋፍ ሥርዓት የሚመራ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ሲሆን አሁን ላይ የፍኖተ ካርታው ዝግጅት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ካስቀመጣቸው ጉዳዮች አንዱ የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን የሚተገብሩ ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማት ለማቋቋምና ለማደራጀት የሚያስፈልጉ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅትን የሚመለከት መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ መሰረት የዓለም አቀፍ ወንጀሎችን የሚደነግግ አዋጅ፣ የእውነት ምህረት እና ማካካሻ ኮሚሸን ማቋቋሚያአዋጅ እና የሌሎች የሽግግር ፍትሕ አላባዎች ፈፃሚ ተቋማት ማቋቋሚያ አዋጆችን የማርቀቅ ሥራ እየተሳለጠ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም በሽግግር ፍትሕ ማእቀፍ የወንጀል ጉዳዮችን የሚያየው ልዩ ችሎት ስልጣንና አሰራርን የሚመሰርተው የሽግግር ፍትሕ ልዩ ችሎት አዋጅ ዝግጅት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስተባባሪነት እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
የሕግ ማዕቀፎቹ ዝግጅት በጉዳዩ ላይ በቂ እውቀትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የሚካሄድ ሲሆን አጠቃላይ ሒደቱ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ነው የተገለጸው፡፡
የህግ ማርቀቅ ሥራው እንደተገባደደ ህዝቡና ባለድርሻ አካላት ዝርዝር አስተያየት የሚሰጡባቸው ሀገር-አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች እንደሚዘጋጁም ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹላይ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
የነዚህ ሕጎች በፍጥነት መውጣት በፖሊሲው ላይ የተመላከቱትን ዓላማዎች ለማሳካት በተለይም የተለያዩ የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን በመጠቀም እውነት ለማውጣት፣ እርቅ የሚወርድበትን አሰራር ለመመስረት፣ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረትን ተግባራዊ ለማድረግ የማካካሻና ተቋማዊ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማከናወን እና በአጠቃላይም የተሟላ ፍትህ ለማስፈን ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡