መጋቢት 17/2013 (ዋልታ) – የኤርትራ መንግስት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማምቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በአስመራ በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የህወሓት የወንጀል ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሀገር በማተራመስ ሥልጣን ለመያዝ የከሸፈ ሙከራ ማድረጉን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት አመልክተዋል::
ቡድኑ ሰሜን እዝን በማጥቃት የመከላከያ አባላትን በጭካኔ በመግደል እና በማፈን በፈፀመው እኩይ ተግባር የፌዴራሉን መንግሥት ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻው እንዲገባ አስገድዷል፡፡
የእዙን ጥቃት ተከትሎ የህወሃት ቡድን በባህር ዳር እና በጎንደር ከተሞች ሮኬቶችን ተኩሷል፡፡
በተመሳሳይም ይህ የህወሃት የወንጀል ቡድን ወደ የኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ሮኮት ተኩሷል:: ይህ ጥቃትም የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ ድንበር አቋርጦ እንዲገባ እና ተጨማሪ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ብሄራዊ ደህንነቱን ለማስጠበቅ እንዲንቀሳቀስ አድርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ ላይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረጉት ውይይትም የኤርትራ መንግስት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማምቷል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል የድንበር አካባቢዎችን ለመጠበቅ ስፍራውን ወዲያው ይረከባል ነው ያሉት::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሁለቱ አጋር ሀገራት መካከል መተማመን እና መልካም የሆነ የጉርብትና መንፈስ መገንባታችንን እንቀጥላለን ብለዋል::
በተለይም ይህን በመተማመን ላይ የተመሰረተ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በትግራይ ክልል እና ኤርትራዊያን ወገኖቻችን መካከል ያለውን መመለስ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡