የእናቶችና የህጻናት ጤናና ስርዓተ ምግብ ሁኔታን ለማሻሻል ያለመ የንቅናቄ መድረክ በጋምቤላ ተካሄደ

የእናቶች፣ የጨቅላ ህጻናትና የህጻናት ጤናና ስርዓተ ምግብ ሁኔታን ለማሻሻል ያለመ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ “የተጠናከረ የጋራ ጥረት ለተመጣጣኝ የጤና ልማት!” በሚል መሪ ቃል በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የተገኙት የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ኡሞድ ኡጅሉ እንደተናገሩት ንቅናቄው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያቀፈ ነው፡፡

በመሆኑም በእናቶች፣ ጨቅላ ህጻናት እና ህጻናት ጤናና ስርዓተ ምግብ እንዲሁም በኤችይቪ ኤድስና ኮቪድ-19 መከላከል ዙሪያ በክልሉ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ያግዛል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንዳሉት በእናቶች፣ በጨቅላ ህጻናትና ህጻናት ጤናና ስርዓተ ምግብ ዘርፍ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በተሰራው ስራ እንደሃገር በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ይሁንና አሁንም በዘርፉ ሀገሪቱ ያልተሻገረቻቸው በርካታ ችግሮች በመኖራቸው እነዚህ በቀጣይ 5 እና 10 ዓመት የጤናው ዘርፍ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተካትተዋል፡፡

ለአብነትም በጋምቤላ ክልል በ2012 ዓ.ም የቅድመ ወሊድ ክትትል 4 ጊዜ እና ከዚያ በላይ ያደረጉ እናቶች ቁጥር 23 በመቶ ብቻ መሆኑን ዶ/ር ሊያ አንስተዋል፡፡

በሰለጠነ ባለሙያ የወለዱ እናቶች ሽፋን 40 በመቶ ላይ ሲሆን የህጻናት ክትባትም መሻሻል ከማሳየቱ በቀር አሁንም ዝቅተኛ ሽፋን እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

መቀንጨርን ከመቀነስ አኳያም በክልሉ የሚያበረታታ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው ችግሩ አሁንም የተቀናጀ ጥረትን የሚጠይቅ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡

የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው በአገር ደረጃ የእናቶች፣ የጨቅላ ህጻናትና የህጻናት የጤና ችግሮች ሳይፈቱ የሚደረግ የልማት ጥረት አይሳካም ብለዋል፡፡

የንቅናቄ መድረኩ ተመጣጣኝ የጤና ልማትን በክልሉ ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላትን የተጠናከረ የጋራ ጥረትን በማስተባበር በችግሩ አሳሳቢነት፣ መንስኤዎችና መፍትሄዎች ላይ ለመምከር ያለመ ነው፡፡

የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከጤና ሚኒስቴር እና ከጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች መሳተፋቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡