የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ክልሉ ለለውጡ አመራር ለሰጠው ድጋፍ ምስጋና አቀረበ

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ህዝብ በራሱ ፍላጎት በመነሳሳት ለብልጽግና ፓርቲ እና ለለውጡ አመራር ለሰጠው ድጋፍ ምስጋና አቀረበ፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት በብሔር ፖለቲካ ሀገርን ሲያተራምስ እና የኢትዮጵያን ህዝብ ሲከፋፍል የነበረውን ጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን በማስወገዳችን ኩራት ሊሰማን ይገባል ሲሉ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሠማ ተናግረዋል።

የጥፋተኛውን ቡድን የተሳሳተ መንገድ አስቀድሞ በመረዳት የጥፋት ሀይሉን በመቃወም ለታገለው የኦሮሞ ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

ከለውጡ በኋላ ወንድማማችነት፣ ሰላም እና ፍቅር እየሰፈነ ይገኛል ያሉት አቶ ፋቃዱ የኦሮሚያ ህዝብ ይህንን ጽንፈኛ ቡድን በመቃወም ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ በቁስና በሞራል ያሳየ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተካሄደው ሰልፉም ይህንን ያሳያል ነው ያሉት።

ሰልፉ ለውጡ እንዲቀጥል እና የለውጡ ባለቤት ህዝቡ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ የገለፁት አቶ ፍቃዱ፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ ለማሳየት የተደረገ ሰልፍ ነው ብለዋል።

አቶ ፍቃዱ አክለውም ከ25 ሚልየን በላይ ህዝብ በፍላጎቱ በሀገሪቱ ላይ እየታየ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ የወጣ እንደሆነ እና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ፅንፈኞችን ለማውገዝ ያለመ በመሆኑ ማህበረሰቡ በተረዳው ልክ ሀሳቡን ሊገልፅ ይችላል ብለዋል።

ለውጡ ከጀመረበት ዕለት አንስቶ በክልሉ እና በሀገሪቱ ለመጣው ለውጥ ንቁ ተሣታፊ ለነበሩት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና የህዝብን ድምፅ የሚወክል እንዲሆን የኦሮሚያ ክልል ህዝብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

(በአድማሱ አራጋው)