የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከ500 ሺህ በላይ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራ ገለጸ

ወ/ሮ ሌሊሴ ዱጋ

የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን የክልሉን የቱሪዝም መዳረሻዎች በማልማት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራ ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ከዘርፉ የሚገኙ ጥቅሞችን ለማሳደግ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ ወሳኔ መሰረት “ክልሉን ለጎብኝዎች ቀዳሚ እና ተመራጭ መዳረሻ ማድረግ” የሚል ራዕይ ሰንቆ መመስረቱን ኮሚሽነሯ ወ/ሮ ሌሊሴ ዱጋ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሰረትም የቱሪዝም ዘርፉ ለሀገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ እድገት የሚኖረውን ሚና ከግምት በማስገባት የዘርፉን ልማት ለማፋጠን ኮሚሽኑ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ኮሚሽነሯ አክለውም በተለይም የቱሪዝም ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ዘርፉ በአገር ልማት የሚጠበቅበትን ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማድረግ የኮሚሽኑ ዋነኛ ትኩረት ነው ብለዋል፡፡

የህበረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ ቱሪዝም ልማት ማህበረሰብ ተኮርና ወጣት መር የሚል መርህ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሁሉም የማህበራዊ ድረ ገፆች #visit_oromia በሚል እንቅስቃሴ የክልሉን የቱሪዝም መስህቦች በስፋት እያስተዋወቀ እንደሚገኝ የገለፀ ሲሆን፣ በቅርቡ በሸገር ፓርክ የቱሪዝም ኤግዚቢሽን እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል፡፡

(በሳሙኤል ሀጎስ)