የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “አብቹ አባ ቢያ” የሚል የገዳ የጀግንነት ስያሜ ሰጠ

“አብቹ አባ ቢያ”

ታኅሣሥ 2/2014 (ዋልታ) የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግንባር ተሰልፈው ሰራዊቱን በመምራት ላስመዘገቡት ድል “አብቹ አባ ቢያ” የሚል የገዳ የጀግንነት ስያሜ መስጠቱን አስታወቀ።

ኅብረቱ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ኅብረት የፈጠረ ማንኛውም አካል የኦሮሞ ጠላት እንደሆነም ወስኗል።

ኅብረቱ ዛሬ ባካሄደው ጉባዔ በከረዩ አባ ገዳ ላይ ጠላት የፈፀመውን ግድያ በጽኑ አውግዟል።

የኅብረቱ ፀሐፊና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ እንዳሉት የኦሮሞ ሕዝብ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለሀገር አንድነት የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው።

“ጠላት ‘ሀገር ፈረሰች’ ብሎ ሲጠብቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር ሰራዊቱን በአካል ተገኝተው በመምራት ሕዝብን ከስጋት ከማላቀቅ ባለፈ የሀገሪቷን ኅልውና ያረጋገጠ ድል እንዲመዘገብ አድርገዋል” ብለዋል።

የመጫ ኦሮሞ አባ ገዳ እና የኅብረቱ አባል አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተመዘገበው ድል የመላው ኢትዮጵያዊያን ድል መሆኑን አመልክተዋል።

“ድሉ የውስጥና የውጭ ጠላት በሀገራችን ላይ የሸረቡትን ሴራ የበጣጠሰ ከመሆኑም ባለፈ የተጀመረውን ዘመቻ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ትልቅ ወኔ የሰነቀ ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገርን ለማዳን ከቤተ መንግስት ወጥተው በግንባር ጦሩን በመምራት በጠላት ላይ ላስመዘገቡት ድልና ጀግንነት የኦሮሞ አባገዳዎች ኅብረት አድናቆትና ምስጋና መቸሩን ገልጸዋል።

“ኅብረቱ በኦሮሞ የጀግና ስያሜ ሞጋሳ መሰረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘አብቹ አባ ቢያ’ የሚል የገዳ ስያሜ ሰጥቷል” ሲሉም ይፋ አድርገዋል።

”ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ኅብረት የፈጠረው ሸኔ የኦሮሞ ጠላት ነው” ሲሉም የኅብረቱን አቋም ገልጸዋል።

ከኦሮሞ ሕዝብ አንድነትና ፍላጎት በተፃረረ መልኩ ከጠላት ጋር የተሰለፉ የሸኔ ታጣቂዎች እጃቸውን ለመንግስትና ለአባ ገዳዎች እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የአርፈን ቀሎ አባገዳ ሸምል አሕመድ በበኩላቸው “በአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ እኩይ ሴራ ተታለው ጫካ የገቡ የኦሮሞ ልጆች ካሉ ተመልሰው ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን ጠላትን ማጽዳት አለባቸው” ብለዋል።

“ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ጥምረት የፈጠረ ማንኛውም አካል የኦሮሞ ጠላት ነው፤ የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት የሞተለትን ዓላማ በመዘንጋት ከጠላት ጋር ማበር ውርደት ነው” ያሉት ደግሞ የኦዳ ሮባ ሲኮ መንዶ አባገዳ አሊይ ሙሐመድ ሱሩር ናቸው።

“በከረዩ አባ ገዳ ላይ የተፈፀመው ግድያ የኦሮሞን ሕዝብ ለማዋረድ ያለመ የጠላት ተግባር በመሆኑ ፍትህ እንፈልጋለን” ብለዋል።

በከረዩ አባ ገዳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ ወንጀሉን የፈፀሙ አካላት በአፋጣኝ ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ደግሞ የቦረና አባገዳ ኩራ ጃርሶ ናቸው ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።