የኦዲት ግኝት የተመዘገበባቸው 39 መስሪያ ቤቶች ተቀጡ

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) የኦዲት ግኝት የተመዘገበባቸው 39 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በገንዘብ እንዲቀጡና ከባድ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲጻፍባቸው ተወሰነ፡፡

በዋና ኦዲተር ባለፉት ሦስት ዓመታት ተመርምረው የኦዲት ግኝት የተመዘገበባቸው ዘጠኝ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የበላይ ኃላፊዎችና የፋይናንስ ዳይሬክተሮች እያንዳንዳቸው በቅደም ተከተል 10 ሺሕ እና 9 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡

በሌሎች 30 ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ላይ ደግሞ ከባድ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲጻፍባቸው መወሰኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የአሶሳ፣ ቡሌ ሆራ፣ ደብረማርቆስ፣ ኦዳ ቡልቱም፣ ባሕር ዳር፣ ሲቪል ሰርቪስ፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶችና የፋይናንስ ዳይሬክተሮች እንዲሁም የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የበላይ ኃላፊዎችና የፋይናስ ዳይሬክተሮች የገንዘብ ቅጣቱ ከተወሰነባቸው ተቋማት መካከል ይገኙበታል፡፡