የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ከራሺያ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ትብብር አባላት ጋር ተወያዩ

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ከራሺያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ትብብር አባላት ጋር ተወያዩ።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከራሺያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ከተውጣጡ የዓለም አቀፍ የቢዝነስ ትብብር አባላት ጋር በተለያዩ የንግድ እና ኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በተለይ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቲክ መናህሪያነቷ ባለፈ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያስመዘገበችው ባለው እድገት የበርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ ላይ ያለች ከተማ መሆኗን የጠቀሱት አባላቱ በመንግስት እና በግል ዘርፍ ትብብር ላይ አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የከተማዋን እድገት በሚያፋጥኑ የቴክኖሎጂ ፣የአገልግሎት ፣የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ለመስራት ያላቸውን የቢዝነስ አማራጮች ለከፍተኛ አመራሮቹ አብራርተዋል።

በአውሮፓ እና አፍሪካ ሀገራት ከ5 ቢሊየን ዶላር በላይ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራታቸውን አባላቱ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱም አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የተለያዩ ኩባንያዎች በከተማዋ በተለይም በዘመናዊና አነስተኛ ዋጋ ባላቸው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመሳሰሉት ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ገልፀውላቸዋል።

በውይይቱ የሚመለከታቸው የከተማዋ ቢሮ እንዲሁም የአዲስ ቻምበር ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በጋራ ትግበራ ቡድን ወደ ተጨባጭ ኢንቨስትመንት መግባት በሚያስችል መልኩ ከስምምነት መደረሱን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።