የከተራ እና ጥምቀት በዓል አስመልክቶ በጃንሜዳ የፅዳት ዘመቻ ተከናወነ

በጃንሜዳ የፅዳት ዘመቻ

ጥር 9/2015 (ዋልታ) ከነገ ጀምሮ የሚከበረውን የከተራ እና ጥምቀት በዓል አስመልክቶ በጃንሜዳ የፍቅር ያሸንፋል ማህበር አባላት የፅዳት ዘመቻ አከናውነዋል፡፡

በፅዳት ዘመቻው ላይ የእስልምና፣ ፕሮቴስታንስት እና ዋቄፈና እምነት ተከታዮች መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡

ጽዳቱን ያከናወንነው ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ወንድምና እህቶቻችን ያለንን ፍቅርና ወገንተኝነት ለማሳየት ነው ያሉት በመርኃግብሩ የተገኙ ተሳታፊዎች አንድነታችንን ልናጠናክር የምንችለው ስንቻቻልና ስንተሳሰብ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

መርኃ ግብሩን ያዘጋጀው የፍቅር ያሸንፋል ማህበር በበኩሉ ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጾ ኢትዮጵያ በርካታ እምነቶች ተቻችለውና ተደጋግፈው የሚኖሩባት አገር መሆኗን አስታውሷል።

በየዓመቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል ሲመጣ ደግሞ የእምነቱ ተከታዮች ያልሆኑ ጭምር ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ወንድሞቻቸው ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት በዓሉ የሚከበርበትን ቦታ በማፅዳት ፍቅራቸውን እንደሚያሳዩም ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች ካስመዘገበቻቸው በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል ተጠቃሽ ነው።

በሱራፌል መንግስቴ