ሰኔ 11/2013 (ዋልታ) – ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማደናቀፍ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና መከላከል ላይ የሚሰራ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲሎማሲ ማዕከል ተመሰረተ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ምሁራን ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና አስመልክቶ ያዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የመሟገት ዓላማ ይዞ የተቋቋመውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲፕሎማሲ ማዕከል ይፋ አድርገዋል።
ማዕከሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚመራ ሲሆን፣ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ተመሳሳይ ማዕከላት እንደሚቋቋሙ ተገልጿል።
ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ዲፕሎማት እንዲሆንና ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በግድቡ ዙሪያ የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያበረክቱ በጎ ተነሳሽነት መፍጠር ማዕከሉ የተቋቋመበት ሌላው ዓላማ ነው።
ማዕከሉ ለብሔራዊ ጥቅም የሚሟገቱ ምሁራንና ተማሪዎችን ማፍራት እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጠንካራ የዲፕሎማቶች መፍለቂያ የማድረግ ራዕይ አለው ነው የተባለው።
በተጨማሪም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚቋቋሙት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላት በተቋማቱ የሚገኙ ተማሪዎችን በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ለማቀራረብ እንደሚያግዙ ተገልጿል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚቋቋሙ ማዕከላት የሚተሳሰሩበት “ናይል ኔሽንስ” የተሰኘ መጠሪያ ያለው ሶፍትዌር በበይነ መረብ የውይይት መድረኩ ላይ ይፋ ሆኗል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በውይይቱ መድረክ ላይ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚገኝበትን ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።