የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ባለስልጣን ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳልተወጣ ተገለጸ

መጋቢት 22/2014 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ባለስልጣን በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት እና ስልጣን በአግባቡ እንዳልተወጣ ገለጸ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ፣ ጥራት እና ቁጥጥርን በተመለከተ የ2012 እና የ2013 በጀት ዓመት በክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ከባለስልጣኑ ኃላፊዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ ባለስልጣኑ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን ጠቁመው መስሪያ ቤቱ እስከ ሚያዚያ 8 ቀን ድረስ የኦዲት ሪፖርት ማስተካከያ እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አቅጣጫ መቀመጡንም ሰብሳቢው አስታውሰዋል፡፡
የፌዴራል ሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በባለስልጣኑ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን መርምሮ በሁለት ወራት ውስጥ ማቅረብ እንዳለበትም ነው ማሳሰቢያ የተሰጠው።
የፍትህ ሚኒስቴርም ከኦዲት ሪፖርቱ አንፃር በባለስልጣኑ የወንጀል ምርምራ በማድረግ የሁሉንም አፈጻጸም ሪፖርት በሁለት ወራት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ ተጠይቋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አራሪ ሞሲሳ በበኩላቸው የባለስልጣኑ ኃላፊዎች የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ምላሽ ያልሰጡ መሆኑን ገልጸው የተሰጣቸውን ስልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ትውልድን ለመቅረጽም ሆነ ለማበላሸት እድሉ በባለስልጣኑ እጅ ላይ መሆኑ ታውቆ ችግሮች በትብብር እንዲፈቱ ሁለንተናዊ ጥረት መደረግ እንዳለበትና ከተቋሙ አመራሮችም ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
ባለስልጣኑ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በኩል በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር ረገድ ችግሮች የሚታዩበት መሆኑንም የቋሚ ኮሚቴው አባላት አንስተዋል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ባለስልጣን የትምህርትና ስልጠና ዋና ዳይሬክተር አንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋሙ የሰው ኃይል፣ የአደረጃጀት፣ የተሸከርካሪ እና የቢሮ ችግሮች እንዳሉበት መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡