የኪዳን መረዳጃ እድር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረገ

መሰከረም 23/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኪዳን መረዳጃ እድር ማኅበር በደባርቅና ዳባት ወረዳ በአሸባሪው የትሕነግ ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 1 ሚሊየን ብር የሚገመት የአልባሳት ድጋፍ አደረገ፡፡
የማኅበሩ አባላት በጭና ተገኝተው ነው ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጅዎች የአልባሳት ድጋፍ ያስረከቡት፡፡
የመረዳጃ እድር ማኅበሩ 625 ብርድ ልብስና የተለያዩ አልባሳትን ያካተተ ድጋፍ ነው ለተጎዱ ወገኖች ያበረከቱ ሲሆን፣ የማህበሩ አባላት በደባርቅ ወረዳ ቦዛ ቀበሌ ተገኝተው ተጎጅ ወገኖችን እንደሚመለከቱና ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስረክቡም ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የኪዳን መረዳጃ እድር ማኅበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበባው ተቀባ፣ አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በንጹሐን ላይ የፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በየትኛውም ዓለም አልተፈፀመም ብለዋል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ የተገኙት የዳባት ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ አቶ ሙሉቀን ፀጋነው በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኪዳን መረዳጃ እድር ማኅበር አባላት ለወገኖቻቸው ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።
በቀጣይ ድጋፍ የሚያደርግ ማንኛውም አካል የዕለት ደራሽ ምግብ፣ የቤት ቁሳቁስና መሰል ድጋፎችን ቢያመጡ የተሻለ መሆኑን ጠቁመው፣ የኅብረተሰቡ ንብረት በመዘረፉና አዝመራውም በመውደሙ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡