የክልሉን ምክር ቤት ጉባኤ ለማደናቀፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው ተገለጸ

አንድነት አሸናፊ

ሐምሌ 29/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚቀጥለው ሳምንት የሚደረገውን የክልል ምክር ቤት ጉባኤ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላት እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የክልሉ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮና ፖሊስ ኮሚሽን ገለጹ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች በወቅታዊ ክልላዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጸጥታ ተቋቱ በመግለጫቸው በክልሉ እያደገ የመጣው አንጻራዊ ሠላም እየሰፈነ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ሁኔታ እንዳይቀጥል የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት የተቋማቱ መሪዎች የክልሉ መንግሥት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተላልፈው የሚገኙ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የክልሉ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አንድነት አሸናፊና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ በርካታ ሥራዎችን ወደ ተግባር ለመለወጥ በህገ መንግሥቱ የተቀመጡ ተግባራትን የክልሉ አስፈጻሚ እና የክልሉ ምክር ቤትም እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ የሚታዩ የጸጥታ ስጋቶች በተለይም የአርብቶ አደሮች አካባቢ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ የከብቶች ዘረፋ፣ የሰው ህይወት መጥፋትና በአካል ላይ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መፍታት ከኅብረተሰቡ ጋር በመነጋገርና በመወያየት አንጻራዊ ሰላም ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ

የጸጥታ ችግር በነበረባቸው የክልሉ አካባቢዎች ሕዝቡን ባሳተፈ ውይይትና ምክክር ችግሮች እየተፈቱ መምጣታቸው ተመላክቷል።

ሸፍተው ወደ ጫካ የገቡ ዜጎች ወጥተው እጃቸውን ለመንግሥት የሰጡበት እና ይዘው የገቡትን መሳሪያ ለመንግሥት ያስረከቡበት እንዲሁም ጥፋታቸው ቀለል ያሉትን ማኅበረሰቡ ምህረት በማድረግ በአካባቢዎች ሰላም መፍጠር መቻሉን እና ይህም እምርታዊ ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሁንም ወጣ ገባ የሚሉ የጸጥታ ስጋቶችን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎችን የክልሉ መንግሥት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ውጤት መገኘት በሁሉም አካባቢዎች የጸጥታ መዋቅሩ፣ አመራሩ፣ ሕዝቡ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች የጋራ ጥረት የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የክልሉ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አንድነት አሸናፊ አንዳንድ አካላት የክልሉ መንግሥት የሚያደርገውን የምክር ቤት ጉባኤ ለማደናቀፍ ህጋዊ ያልሆኑ ሰልፎችን ለማድረግ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ጥሪ እያደረጉ መሆኑ ተደርሶበታል ብለዋል።

በተለይም በቦንጋና አካባቢው፣ በሌሎች አካባቢዎች ሕዝቡን ለማደናገር ግጭት ሊያነሳሳ የሚችል፣ በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር በሚያደርግ መንገድ በሕዝቦች መካከል ጥላቻን ለመዝራት በየማኅበራዊ ሚዲያ ስሜት ቀስቃሽ ተግባራት እየፈጸሙ ያሉ ግለሰቦች እንዳሉም አመላክተዋል። ይህ ህገ ወጥ ተግባር በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት እንደማይኖረው ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡

የትኛውም አይነት ጥያቄ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ መደረግ አለበት ያሉት ኃላፊው ከዚህ ውጭ ያለ ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረግ እንቅስቃሴ የክልሉ መንግሥት አይታገስም ብለዋል።

ያልተፈቀዱ ህጋዊ ያልሆኑ የትኛውንም አይነት ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲባል የህግ የማስከበር ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ህግ የሚያስከብሩ አካላት ህግ ያስከብራሉ የአስተዳደር አካላትም ህጋዊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን የማስቆም ተግባር መፈጸም አለባቸው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳይያስ በበኩላቸው ክልሉ ከምስረታ ጀምሮ አንጻራዊ ሠላሙን አስጠብቆ እየሄደ ያለ ክልል መሆኑን አመላክተዋል።

ኮሚሽነሩ የክልሉን ሠላም ለማደፍረስ የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረጉም በጸጥታው አካል ማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል።

አሁን የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች እየተላለፉ እንደሚገኙም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

እነዚህ መልዕክቶች የተለያዩ የተደበቁ ቡድኖችን ፍላጎት የማሳካትና የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች እንደሆኑም ተደርሶበታል ብለዋል።

ፖሊስ የሕዝቡን ሠላምና ደኅንነት የመጠበቅና የሕዝቡን ህይወት እና ንብረት ከየትኛውም አደጋ የመጠበቅ ሙሉ ኃላፊነት የተሰጠውና ያለበት በመሆኑ የትኛውንም ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የማይታገስ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ የተለየ እንቅስቃሴዎችን ካየ ከጸጥታው አካል ጎን በመሆን እንደተለመደው ትብብሩን አጠናክሮ የክልሉን ሠላም ማስጠበቅ ይገባዋል ሲሉ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

ሁለቱም የሥራ ኃላፊዎች በመግለጫቸው በክልሉ የመጣውን አንጻራዊ ሠላም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ ሕዝቡ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ አካላት ጋር ተባባሪ እንዳይሆን እንዲሁም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን በማጋለጥ ትግል እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።