የክልሉን ቱሪዝም ለማነቃቃት በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የክህሎት ስልጠና ተሰጠ

ግንቦት 13/2014 (ዋልታ) በአፋር ክልል ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላት በቂ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው በማድረግ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ድርሻ ማሳደግን ታላሚ ያደረገ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው በኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ የተሰጠ መሆኑ
ተገልጿል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር አማካሪ ይስፋልኝ ሀብቴ ለአፋር ክልል የቱሪዝም ዘርፍ ተዋናንያን የተሰጠው የእውቀትና ክህሎት ስልጠና በቱሪዝም ዘርፍ ዙሪያ ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ እይታ ለማሻሻል በጎ ሚና አለው ብለዋል፡፡

ክልሉ በኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው የቱሪዝም መዳረሻዎችን በውስጡ የያዘ በመሆኑ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የተሰጠው የእውቀትና ክህሎት ስልጠና አጠቃላይ የኢኮ-ቱሪዝም ዘርፉን እንደሚያሳድገው ታምኖበታልም ነው የተባለው፡፡

የአፋር ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴ በጦርነት እና በኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ ተቀዛቅዞ የነበረ በመሆኑ ስልጠናው ሴክተሩን ከማነቃቃት ባለፈ የቱሪዝም ዘርፉን ኢኮኖሚያዊ እይታ የሚያሻሽል እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

ስልጠናው በዋናነት በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማራው የሰው ኃይል በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ሲሆን የቱሪዝም ዘርፉ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ህይወት የሚቀይርና ለዜጎችም ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥር እንደሚሆን ሰፊ ግንዘዛቤ እንዲጨብጡ እንዳስቻላቸው ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፀጥታና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ጉዞ ላይ ትገኛለች፡፡

ደረሰ አማረ (ከሰመራ)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW