የክልሉን ነዋሪዎች በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ተገለፀ

ጥር 16/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የክልሉን ነዋሪዎች በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከዳዉሮ ዞን ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ሁኔታ በታርጫ ከተማ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ የዞኑ ነዋሪዎች ክልሉ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ክልል በመሆኑ ፍትሃዊነት እና እኩል ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንዳለበት አሳስበው በዞኑ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መጓተት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያስከተለ መሆኑን አብራርተዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የዳዉሮ ካምፓስ፣ የዋካ ሆስፒታል፣ የመንገድ መሠረተ ልማት እንዲሁም በሹመት፣ በዝውውር እና በቅጥር የሚታዩ ክፍተቶች ማስተካከያ እንደሚያስፈልጋቸው አንስተዋል።
በተለይም በክልሉ ሕገ-መንግሥት የተገለጸው የማዕከላት ጉዳይ በቶሎ መፈታት እንዳለበትም ጠይቀዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ/ር) ከሁሉም በፊት ነዋሪዎች የአካባቢያቸውንም ሆነ የክልሉን ሠላም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመጠበቅና በማስጠበቅ ልማታችንን እያረጋገጥን እንድንሄድ የሚያግዙ ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የመንግሥት ተቋማት ኢፍትሃዊ አሰራርን በማስቀረት ለዜጎች ተጠቃሚነት የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ማዘመን እንዳለባቸው ማስረዳታቸውን የደሬቴድ መረጃ አመልክቷል።
የመሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት በእኛ ጎታች ምክንያት ተጀምረው የቆዩትን የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል ለአገልግሎት ማብቃት ወሣኝ መሆኑን አስረድተዋል።
የተፈጥሮ ሀብቶች በጀት ሊሆኑ በሚችሉበት አግባብ ግልጽ የሆነ የአሰራር ማዕቀፍ መዘርጋት፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።
የማዕድናት ሀብት አጠቃቀም ላይ የሚታየው ቅሬታ እና ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር ተያይዞ የዞኑን ከፍተኛ አመራሮች የማንኳሰስ ተግባራት ሊወገዝ እንደሚገባም ተገልጿል።