የክልሉን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በተሰራ ሥራ አበረታች ውጤት መመዝገቡ ተጠቆመ

የካቲት 10/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የክልሉን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ሰፊ የውጭ ምንዛሬን ለማምጣት እና የሥራ እድል ለመፍጠር ባለፉት 6 ወራት ውስጥ በተሰራ ሥራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ለጨፌው ባቀረቡት ሪፖርት የክልሉን ህዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እና ምርትና ምርታማነትን ተደራሽ በማድረግ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ሰፊ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡

ክልሉ በስፋት እየሰራበት በሚገኘው የስንዴ ምርት በግማሽ ዓመቱ በክረምት እርሻ በተሰራው ስራ ከ64 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

የክልሉን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመፍጠር የግብርናውን ዘርፍ በክላስተር እና መካናይዜሽን ለማድረግ እስካሁን በተሰሩ ስራዎች 4 ነጥብ 54 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በክላስተር እርሻ የለማ ሲሆን ከ4ሺሕ 100 በላይ ትራክተሮች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉ ተጠቁሟል።

በሚልኪያስ አዱኛ