ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት የህዳሴው ግድብ ግንባታ እንዳይሳካ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ለዓመታት ጫና ሲያደርጉ ቆይተዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ መሆኑን የተናገሩት አቶ አሻድሊ፣ መንግሥትም ይህን አቋሙን ሳይቀይር ለዓመታት ዕውነታውን ይዞ መታገሉን አስረድተዋል።
መንግሥትና ሕዝብ ባደረጉት ጥረት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ይሄም ኢትዮጵያውያን ከተባበበሩ የማያልፉት ፈተና እንደሌለ በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ቀጣይ ስራዎችን ለማከናወን ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝብና መንግስት ግድቡ ሙሉ ለሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናከሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ዛሬ ላይ የተገኘው የድል ብስራት የኢትዮጵያን ልማትና እድገት የማይፈልጉ ኃይሎችን ቅስም የሚሰብር መሆኑንም አስረድተዋል።
የሀረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በተመሰሳይ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት የክልሉ ህዝብና መንግስት ቀሪ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ድጋፉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በማንኛውም ፈታኝ ወቅት ህዝብ ከተባበረ ማሳካት የማይችለው ግብ እንደሌለ የተናገሩት፤ርዕሰ-መስተዳደሩ ለዚህ ድል ሲጓጉ የነበሩ መላው ኢትዮጵያዊያንም ህብረታቸውንና አንድነታቸውን አጠናክረው እንዲሰሩም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የአፋር ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡