የክልል ኢኮኖሚ አካውንት የአሠራር ሥርዓት ማረጋገጫና ማቋቋሚያ ወርክ ሾፕ እየተካሄደ ነው

ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) – የክልል ኢኮኖሚ አካውንት የአሠራር ሥርዓት ማረጋገጫና ማቋቋሚያ የሙከራ ግምቶች ማጠናከሪያ ወርክ ሾፕ እየተካሄደ ነው ::

በፕላንና ልማት ኮሚሽን የብሔራዊ ኢኮኖሚ አካውንት ዳይሬክቶሬት በኩል ተዘጋጅቶ የክልል ኢኮኖሚ አካውንት የአሰራር ስርዓት ማረጋገጫና ማቋቋሚያ የሙከራ ግምቶች ማጠናከሪያ ዙሪያ የሚደረገው ወርክ ሾፕ በትናንትናው እለት ተጀምሯል፡፡

ከአዲስ አበባ እና ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ተሳታፊዎችን ጨምሮ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ፣ ከሲዳማ፣ ከአማራ፣ ከአፋር፣ ከቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ከጋምቤላ፣ ከሱማሌ እና ከሐረሪ ክልሎች ከመጡ የክልል ኢኮኖሚ አካውን ዳይሬክተሮችና ባለሞያዎች ጋር የሚደረገው ወርክሾፕ ለ10 ቀናት የሚቆይ ነው፡፡

በወርክሾፑ ላይ የኢፌዲሪ ፕላንና ልማት ኮሚሽን የብሔራዊ ኢኮኖሚ አካውንት ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ደምስስ የክልል ኢኮኖሚ አካውንት የአሠራር ሥርዓት ማረጋገጫና የተካሄዱ የሙከራ ጥናቶችን  ማጠናከሪያ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በዚሁ ማብራሪያቸው የተቀናጀ እና ወጥ የክልል ኢኮኖሚ አካውንት አሠራር መንገዶችን ያነሱ ሲሆን፣ አያይዘውም የተቀናጀ እና ወጥ የክልል ኢኮኖሚ አካውንት አሠራር መኖሩ ለምን ያስፈልጋል የሚለውንም አብራርተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ የክልል ኢኮኖሚ አካውንቱ አስፈላጊነት ላይ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ፖሊሲ ለመቅረጽ፣ የክልል ኢኮኖሚን ለመቆጣጠር ለምርምር እና ትንታኔ ጠቀሜታ ያለው ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ግብአት ለማግኘት የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በክልሎች መካከል ያለውን ንጽጽር ከብሔራዊ አካውንት ጋር ለመመዘን እንደሚጠቅም ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ጠቁመዋል፡፡