የክልሎች የፍልሰት ትብብር ጥምረት ምስረታ በመከናወን ላይ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – የክልል የፍልሰት ትብብር ጥምረት በጎንደር፣ አዳማና ይርጋለም ከተሞች መመስረቱን በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጥምረቱ ምስረታ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ተከትሎ ክልሎች የየራሳቸውን የፍልሰት ትብብር ጥምረት እንደሚመሰርቱ በተገለፀው መሰረት የተከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡

በምስረታው በየክልሉ የሚገኙ ቢሮዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሲቪል ማህበራት ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን፣ በመድረኩም የትብብር ጥምረቱ  መመስረቻ መመሪያዎችና የ6 ወር እቅድ ታቅዶ የየክልሉ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ምስረታው ተከናውኗል።

የትብብር ጥምረት ምስረታው በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር ጠቀሜታቸው የጎላ ከመሆኑ ባሻገር ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ፍልሰትን ከማስተዳደርና መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰት ከመከላከል፣ ከመቆጣጠርና ተጎጂዎችን መልሶ ከማቋቋም አኳያ የየራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል ይህ የምስረታ ሂደት በሌሎች ክልሎችም የሚቀጥል መሆኑን ከጠቅላይ ዐቃቤ  ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡