የክረምቱ ዝናብ ከመጠናከሩ ጋር ተያይዞ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ተባለ

ሐምሌ 25/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ልዩ ቦታው አማኑኤል ሆስፒታል አካባቢ የደረሰው ጉዳት ተጨማሪ ጥፋት እንዳያስከትል እየተደረገ ያለው ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።

በትናንትናው ዕለት በዚሁ ቦታ የፍሳሽ ቦዮች በግንባታ ተረፈ-ምርት በመደፈናቸው እና በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ ገንፍሎ የወጣ ጎርፍ በመጋዘን ቤት ውስጥ ተጠራቅሞ የመጋዘኑን አንዱን የግንብ ግድግዳ በመናድ በትናንትናው ዕለት በስምንት ቤቶች የሚኖሩ 30 ቤተሰቦች ላይ ጉዳት በማድረስ ለሁለት ሰዎች ኅልፈት ምክንያት መሆኑ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ በዛሬው ዕለት ጉዳቱ የደረሰበትን ቦታ በአካል ተገኝተው በመመልከት ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች አጽናንተዋል።

ዝናቡ ተጠናክሮ መቀጠሉን ግምት ውስጥ በማስገባት ጎርፉ ቀጣይ ጉዳት እንዳያስከትል የእሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የጀመሩትን ሕይወት አድን ርብርብ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና የተጀመሩ የመፍትሔ እርምጃዎች በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲደረጉ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሐ በበኩላቸው ቦታው ቀደም ሲል በስጋትነት ከተለዩት አካባቢዎች ውስጥ የተካተተ እንዳልነበረ ነው የጠቆሙት።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የተደፈኑ የፍሳሽ ቱቦዎች ጠረጋ ሥራ ከማከናወን በተጨማሪ የማሽነሪ አቅርቦትን በመጨመር አፋጣኝ ጉዳቱን የመቀነስ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሞገስ ጥበቡ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት ክረምቱ እያየለ በመምጣቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገቢውን የመከላከል ተግባር እንዲያከናውኑ፣ ኅብረተሰቡም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ መቅረቡን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።