የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን ጀግንነት የሚዘክረው ሐውልት ተመረቀ

ጥር 22/2014 (ዋልታ) ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ክብር በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው ታላቅ ገድል ከፈፀሙ ጀግኖች መካከል አንዱ የሆኑት ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን ጀግንነት የሚዘክር ሐውልት ዛሬ በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ተመርቆ ለዕይታ በቅቷል፡፡
በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናንት ጄነራል ይልማ መርዳሳ፣ የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ቤተሰቦችና የሥራ ባልደረቦች፣ የኢትዮጵያ መከላከያና አየር ኃይል አመራሮችና አባላት እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡
ኮሎኔል በዛብህ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ ታላላቅ ጀብዱዎችን በመፈፀም ስመ ጥር ከሆኑ ተዋጊ አብራሪዎች መካከል አንዱ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
“እኛ ብንሞት ሌላ ሰው ይተካናል፤ መተኪያ የሌላት ኢትዮጵያ ከሞተች ግን ተተኪው ትውልድ ስለሚሞት ዋጋ አይኖረውም” በሚለው ንግግራቸው የሚታወቁት ኮሎኔል በዛብህ ከሶማሊያ ወረራ ጀምሮ እስከ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ድረስ ተሰልፈው ግዳጃቸውን በአግባቡ የተወጡ የሰማይ አርበኛ ናቸው፡፡
በፍስሃ ጌትነት (ከሆሳዕና)