የኮሚሽኑ ሠራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት 51 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ

ነሃሴ 05/2013 (ዋልታ) – የጉሙሩክ ኮሚሽን አመራሮች እና ሠራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት 51 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ፡፡
ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር የኮሚሽኑ አመራሮች እና የዋናው መስሪያ ቤት ሰራተኞች ደም በመለገስ ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል፡፡
በደም ልገሳው ወቅት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንደገለፁት÷ ከኮሚሽኑ ሰራተኞች እና አመራሮች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚሆን 51 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል ብለዋል፡፡
ደጀን ለሆነው የመከላከያ ሰራዊት ገንዘባችንን አንሰስትም÷ የላቀ ስጦታ የሆነውን ደማችንንም ለመለገስ ዛሬም ነገም ወደኋላ አንልምም ነው ያሉት፡፡
የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽር አቶ አዘዘው ጫኔ በበኩላቸው÷ ከስጦታዎች ሁሉ ውዱን እና በገንዘብ የማይተመነውን ደም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በመለገሳቸው ብሎም ደመወዛቸውን ጭምር በመስጠታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
የህግ ማስከበር ዘመቻው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መናገራቸውንም ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡