የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክን በአፋጣኝ ወደ ሥራ ለማስገባት አስፈላጊው ርብርብ እንደሚደረግ ተገለጸ

የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ

ታኅሣሥ 4/2014 (ዋልታ) የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክን በአፋጣኝ ወደ ሥራ ለማስገባት ግብርኃይል ተቋቁሞ አስፈላጊው ርብርብ እንደሚደረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።

በኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ የተመራው የአመራሮችና የሰራተኞች ልዑክ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ዝርፊያና ውድመት የደረሰበትን የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅት የልዑክ ቡድኑ የፓርኩን የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የማምረቻ ሼዶች፣ የኬሚካል ማጣሪያ እና ሌሎች በፓርኩ ውስጥ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩና በሽብር ቡድኑ ዝርፊያና ውድመት የደረሰባቸውን ቦታዎች ተዟዙሮ ተመልክቷል።

በዚህም የፓርኩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የቢሮ እቃዎችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተሞች፣ የአምራች ኩባንያዎች ቢሮዎችና ቁሳቁስ፣ ለኤክስፖርት የተዘጋጁ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች፣ የምርት ማከማቻ መጋዘኖች፣ ለምርት የተዘጋጁ ጥሬ እቃዎች፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ሌሎች በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁስ ዝርፊያና ውድመት እንደደረሰባቸው ታውቋል።

በጉብኝቱ ወቅትም የፓርኩ ስራ አስኪያጅን ጨምሮ በፓርኩ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ባለሀብቶችና የተለያዩ ድርጅቶች ስራ አስኪያጆች ከኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅትም የደረሱ ጉዳቶችን ማጣራትና የጉዳት መጠኑን ማወቅ እንዲሁም በአፋጣኝ ወደ ሥራ መግባት የሚቻልባቸው አማራጮችን መመልከት የሚሉ ነጥቦች ተነስተዋል።

ስራ አስፈፃሚው በጉብኝቱ ወቅት በአሸባሪ ቡድኑ የደረሰው ዝርፊያና ውድመት አሳፋሪና እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸው የሽብር ቡድኑ ለሀገር እድገት ፀር መሆኑን በግልፅ ያሳየበት ተግባር ነው ብለዋል።

ፓርኩን በአፋጣኝ ወደ ስራ ለማስገባት ግብርኃይል ተቋቁሞ አስፈላጊው ርብርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ፓርኩና ንብረቶች ላይ በደረሰው ጉዳት እጅግ ማዘናቸውን የገለፁት አምራች ድርጅቶቹና ኃላፊዎቻቸው ሥራቸውን በአፋጣኝ ለመጀመርና ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ ለመላክ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ለዚህም አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ መግለፃቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።