የኮሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሳተፉ ተጠየቀ

የካቲት 11/2014 (ዋልታ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የኮሪያ እውቅ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዮክሂን ጋር ተወያይተዋል፡፡

የኮሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የደረሰበትን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ወደ ነበረበት ለመመለስ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና የዘርፉን ውጤታማነት በተሻለ መንገድ ለማስቀጠል ሚናው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም መንግሥት በአምራች ዘርፉ ለመሰማራት ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ኮሪያዊያን ኩባንያዎችና ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መጥቀሳቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዮክሂ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኮሪያዊያን አምራቾች እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍ በማድነቅ አሁንም እያጋጠማቸው ያለውን ችግሮች በጋራ በመሆን እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡