የኮቪድ-19 ተፅዕኖን ለመቀነስና በሽታውን ለመከላከል መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው- አቶ ደመቀ መኮንን

ሚያዝያ 06/2013 (ዋልታ) – የኮቪድ-19 ተፅዕኖን ለመቀነስና በሽታውን ለመከላከል መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ሞኤቲ ሺዲ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ ኢትዮጵያ ኮቪድ-19ን ለመከላከል እያደረገች ያለው ጥረትና በአፍሪካ የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም ውጤታማ መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ፣ የኮቪድ-19 ተፅዕኖን ለመቀነስና በሽታውን ለመከላከል መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዳይሬክተርዋ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር የረጅም ጊዜ አጋርና የትኩረት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ ድርጅቱ በጤና ዘርፍ ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡