ሐምሌ 08/2013 (ዋልታ) – የኳታር ከፍተኛው የወተት ምርት አቅራቢ ድርጅት ባላድና የምግብ ኢንዱስትሪ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጥምረት ለመሥራት እንደሚፈልግ ተገለጸ።
በዶሃ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ አዘጋጅነት በኳታር በወተትና የወተት ምርት አምራች ታዋቂ የሆነው ባላድና የምግብ ኢንዳስትር የተባላ ኩባንያ በኢትዮጵያ በዘርፉ ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድል በተመለከተ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ከግብርና፣ ከንግድና ኢንዳስትሪ ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች በውይይቱ ተሳትፈዋል።
በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በተመለከተ ሰፊ ገበያ ፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች እና በመንግስት በኩል ሊደረጉ የሚችሉ ድጋፎችን አስመልክተው ለድርጅቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የባላድና ድርጅት የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው የድርጅታቸውን ልምድና ይዘት ገለጻ በማድረግ ከውይይቱ በቂ መረጃ ማግኘታቸውንና በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት ለማድረግ እና ከመንግስት ጋር በጥምረት ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ሃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በኳታር ላይ የገልፍ አገሮች ማዕቀብ መጣላቸውን ተከትሎ የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱን የወተት ፍላጎት 90 ከመቶ እየሸፈነ የሚገኝ ግንባር ቀደም ድርጅት መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በሁለቱም ወገን በኩል የኢንቨስትመንት መረጃ መለዋወጡ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው ፤ ድርጅቱ ወደ ሥራ ይገባ ዘንድ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡