የወላይታ ዞን የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣብያ ተመረቀ

ነሀሴ 20/2013 (ዋልታ) – የወላይታ ዞን የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣብያ በዛሬው ዕለት ተመረቀ፡፡
ቴሌቪዥን ጣብያው በዞን ደረጃ ሲቋቋም በኢትዮጵያ የመጀመርያ ሲሆን የትምህርት ሚኒስትር ሳሙኤል ኡርካቶ እና የመገናኛ ብዙሀን ባለስጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅን ግዛው ተስፋዬ ጨምሮ የክልል እና የዞኑ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተመርቆ በይፋ ስራውን ጀምሯል።
ቴሌቪዢኑ በአከባቢው መቋቋም የአከባቢውን ብሎም የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በማሳደግ በኩል ሚናው የጎላ እንደሚሆን ነው የተነገረው።
በተለይም አከባቢው በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ ከመሆኑም ባሻገር በተለያዩ ባህላዊና ጥንታዊ እሴቶች የበለፀገ በመሆኑ በአከባቢው ላይ ያለውን ሀብት በማስተዋወቅ ከፍተኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ንቃት ያመጣል ተብሏል።
ጣብያው መረጃዎችን ከቴሌቪዥን ስርጭት በተጨማሪ በማህበራዊ ድረ ገፅ፣ በበይነ መረብ እና ባዘጋጀው የስልክ መተግበርያ አማካኝነት መረጃዎችን እንደሚያደርስ ተጠቁሟል።
ጣብያው በሶስት ቋንቋ ማለትም በዋላይተኛ፣ በአማርኛ እና በኢንጊሊዘኛ መረጃዎችን የሚያደርስ ሲሆን ከሌሎች አጎራባች ዞኖች ጋር እንደሚሰራ የተገኙ መረጃዎች አመላክተዋል።
የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ እንድርያስ ጌታ (ዶ/ር) የወላይታ የማህበረሰብ ቴሌቪዥን የማህበረሰብ መነቃቃት በመፍጠር ዞኑን እና ሌሎች አጎራባች ዞኖችን የበለጠ በማስተሳር የህዝቦችን አንድነት በመገንባት ትልቅ ሚና ይኖሯል ነው ያሉት።
በተለይም አሁን ወቅቱ የኢትዮጵያን አንድነት እጅጉንም የሚያስፈልግ በመሆኑ ጣብያውም ሆነ በጣብያው የሚሰሩ የሚዲያ ባለሞያዎች ይህን ከግምት በማስገባት በሀላፊነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
(በሚልኪያስ አዱኛ )