ሐምሌ 28/2013 (ዋልታ) – የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ሠራተኞች የአሬንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈው በዞኑ ታቅዶ እየተከናወነ በሚገኘው በክረምት በጎ አድራጎት የስራ ዘመቻ ላይ በመሣተፍ የአንድ አቅመ ደካማ ግለሰብ ቤት የማደስ ተግባር አከናወኑ።
የአሬንጓዴ መርሃ ግብርና የበጎ አድራጎት ተግባር የተከናወነው በወላይታ ዞን የጤና መምሪያ ሴክተር ባለሙያዎችና በዞኑ የጠበላ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፕታል ባለሙያዎች በጋራ በመሆን ነው።
የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አሳምነው አይዛ እንዳሉት የአሬንጓዴ አሻራ በማኖር ለመጪው ትውልድ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ማለፍ ከሁሉም ዜጎች የሚጠበቅ ተግባር ነው።
ህብረተሰቡ ችግኝ የመትከል ባህል በማዳበር በአየር ንብረት ለውጥ ከሚመጡ በሽታዎች ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
በመርሃ -ግብሩ የክቡር እንግዳ በመሆን የዕለቱን ፕሮግራም ያስጀመሩት በወላይታ ዞን የብልጽግና ጽህፈት ቤት የፓለቲካ ርዕዮተዓለም ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዮሐንስ በየነ በበኩላቸው በሀገር ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሃሳብ አመንጭነት የተወጠኑ ዕቅዶች በዞኑ በተለያዩ አደረጃጀቶች እተተገበሩ ይገኛሉ።
በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢያቸው የአሬንጓዴ አሻራቸውን በማሳረፍ ታሪክ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
በ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመት በዞኑ በክረምት ወራት በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀው ይህም በአንድነት ከቆምን የትኛውንም ጠላት ማንበርከክና ማሸነፍ እንደሚንችል መሣያ ነው ብለዋል።
በችግኝ ተከላና በጎ አድራጎት ስራ ላይ የተሳተፉ የዞኑ ጤና መምሪያ እንዲሁም የሆስፒታሉ አመራሮችና ሠራተኞች አገራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በክረምት ዝናብና በበጋ ፀሐይ የሚፈራረቅባቸውን አቅመ ደካሞች ቤት በማደስ ዕገዛ በማድረጋቸው የህሊና እርካታ ማግኘታቸውንም አክለው ገልፀዋል።
እግረ-መንገዳቸውን ወደ ስፍራው ያቀኑት የአካባቢው ተወላጅ ባለሃብት የሆኑት አቶ ተስፋዬ ማርቆስ ሰራተኞቹ እያበረከቱ ባሉት በጎ ስራ ተነሳስተው የ10 ሺህ ብር ቼክ ለተረጂው ግለሰብ አበርክተዋል።
በወላይታ ዞን ጠበላ ከተማ አስተዳደር ነዋሪ የሆኑት በደሳሳ ጎጆ ከቤተሰባቸው ጋር ለብዙ ጊዜያት መሰቃየቱን ተናግሯል።
አሁን ሰለተደረገለት እርዳታ በውኑ ለማመን መቸገሩን ገልፆ ለሰራተኞቹ ምስጋና አቅርበዋል ሲል የዘገበው የወላይታ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።