ሰኔ 06/2013 (ዋልታ) – የወልቂጤ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት የተገኙት የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ለማ በ2013 ዓመተ ምህረት ለሚደረገው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ፓርቲው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የከተማውን ህብረተሰብ ያነሷቸውን የልማት ጥያቄዎች ከመመለስ አንፃር አበረታች ስራዎች መሰራቱን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ለምርጫው እንቅስቃሴ ሲያደርግ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ የመጀመሪያ ግብ ማስቀመጡን ተናግረው ለዚህም የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ፓርቲው አብላጫ ድምፅ አግኝቶ መንግሥት ለመመስረት እየሰራ መሆኑን ተናግረው ፓርቲው ከተመረጠ በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና እንዲመጣ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዜጎች ዋጋ ከፍለው ያመጡትን ለውጥ በተሻለ መልኩ የሚያስቀጥል ፓርቲ ነው ያሉት አቶ ክፍሌ በማህበረሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችም እንዲመለሱ ይሰራል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ አብድልሰመድ የከተማው ህብረተሰብ ለፓርቲው ያለው ድጋፍ የሚያስደስት መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የከተማውን ህብረተሰብ ያነሷቸውን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታቱ ላይ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።
ከ165 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ192 በላይ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በመሰራት ላይ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ላይ መብራት ዝርጋታ፣ የዲችና የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የወጣቶች ማዕከል ግንባታ፣ የአስፓልት መንገድና ሌሎችም የልማት ስራዎች መሰራታቸውና በሂደት ላይ ያሉ መኖራቸውን ተናግረው ሌሎችም የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የልማት ስራዎችን ለማደናቀፍና ምርጫውንም ለማስተጓጎል የተለያዩ አጀንዳ ያላቸው አካላት ስለሚኖሩ የከተማውን ሠላም ከማስጠበቅም ባለፈ ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረመስቀል በበኩላቸው በሃገር አቀፍ ደረጃ ብሎም በከተማው የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ፓርቲው መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግናን በመወከል ለተወካዮች ምክር ቤትና ለክል ምከር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በበኩላቸው ፓርቲው ህብረ-ብሔራዊነት የሚያቀነቅን፤ ሁሉንም በእኩል የሚያይ የፖለቲካ ዕሳቤ ያለው መሆኑን ገልፀው በልማት ዘርፉም በእኩል ተጠቃሚ እንዲሆን የሚሰራ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ብልጽግና ካሸነፈ ለማህበረሰቡ ለውጥ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
የከፋፍለህ ግዛ የፖለቲካ አሻጥር ሃገሪቱ አሁን ላይ ዋጋ እያስከፈላት ቢሆንም ፓርቲው በብቃት እየሰራ ነው ያሉት ዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ፓርቲው ይህንን ችግሮች በብቃት በመወጣት ታላቋን ኢትዮጵያ የሚገነባ በመሆኑ መራጩ ህዝብ ብልጽግናን ቀዳሚው ምርጫ ቢያደርግ ከምንም በላይ ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉም በቅስቀሳው ወቅት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በውይይቱ የተገኙት የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላትም ፓርቲው በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆኖ የሰራቸው ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረው በዋናነትም ሃገራዊ ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልፀዋል።