ጥር 20/2014 (ዋልታ) የወራቤ ዩኒቨርሲቲ በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት ለደረሰበት የወልዲያ ዩኒቨርሲቲን ሥራ ለማስጀመር የሚሆን ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ዩኒቨርሲቲው ካደረጋቸው ድጋፎች መካከል ኮምፒዩተሮች፣ የጽሕፈት መሳሪያዎች፣ ፈርኒቸሮች እንዲሁም ለተማሪዎች መማሪያና መመገቢያ የሚያገለግሉ ቁሳቁስ ይጠቀሳሉ።
የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑም ተገልጿል።
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ ከድር ሽፋ ድጋፉ ዩኒቨርሲቲው ወደ መደበኛው የመማር ማስተማሩ ሂደት በቅርቡ እንዲመለስ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።
የወልዲያ ዩኒቨርሲቲን በሙሉ አቅሙ ሥራ ለማስጀመር ወራቤ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ/ር) ለድጋፉ ምስጋና ማቅረባቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።