የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች  በመዲናዋ  አቀባበል ተደረገላቸው

ሐምሌ 5/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማስጀመር ከየክልሉ ለተውጣጡ ወጣቶች አቀባበል አድርጓል።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመዲን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማኅበራዊ መስተጋብርን ለማሳደግ፣የወጣቱን ስብዕና ለመቅረፅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

በተለይ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የሰሩት የበጎ ፍቃድ ሥራ የሚመሰገን መሆኑን ጠቅሰው አገልግሎቱ ተጠንክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አንስተዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር  የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ  ኃላፊ ሂክራም አህመዲን በበኩላቸው አባቶቻችን ትላንት በሰሩት ሥራ ዛሬ እየተጠቀምን እንደሆነው ሁሉ እኛም ለነገው ትውልድ ተጋግዘን ልንስራ ይገባል ብለዋል።

የበጎ ፍቃድ ሥራ ደግሞ ለነገው ትውልድ አሻራ የምንኖርበት ነውና ይህን ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 19 ሚሊየን ወጣቶች ይሳተፋሉ መባሉ ይታወሳል።

በትእግስት ዘላለም