የወንጪ ደንዲ አገናኝ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሆነ ተገለጸ

ሰኔ 17/2013 (ዋልታ) – የወንጪ ደንዲ አገናኝ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶክተር አብረሃም በላይ ገለጹ።

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶክተር አብረሃም በላይን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የፕሮጀክቱን አገናኝ መንገዶች የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።

ከ3 ወራት በፊት የተጀመረው የፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር አብረሃም ገልጸዋል።

በዚህም ከክረምት በፊትና በክረምት ወራት መሰራት ያለባቸው ስራዎች በእቅድ ተለይተው በመተግበር ላይ ናቸው ብለዋል።

የእስካሁኑ የፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደትም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ዋና አስተባባሪው ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የአገናኝ መንገድ ግንባታው እስከ 120 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እንደሆነም ተጠቁሟል።

የወንጪ ደንዲ የኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት፣ በውስጡ የመዝናኛ ስፍራዎችን ጨምሮ የማራቶን መሮጫ መንገዶችንና የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የያዘ እንደሆነ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ አንድ ዓመት በማይሞላው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ግንባታው በፍጥነት እየተሰራ እንደሚገኝ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።