የወገን ጦር በምስራቅ አማራና አፋር የያዘውን ቦታ አፅንቶ እንዲቆይ ታዘዘ

ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) የወገን ጦር በምስራቅ አማራና አፋር ወረራ የፈፀመውን አሸባሪው ትሕነግ በመደምሰስና ጠራርጎ በማስወጣት አሁን ላይ የያዘውን ቦታ አፅንቶ እንዲቆይ መንግሥት ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ለዚህ ውሳኔ 3 መሰረታዊ ጉዳዮች መወሰዳቸውን አንስተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም መከለከያ ሰራዊቱ በትግራይ በነበረበት ጊዜ የተፈፀመበትን ክህደት መነሻ በማድረግና ካለፈው መማር ስለሚያስፈልግ የሚለው አንዱ ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት የሽብር ቡድኑ የተገደሉበትን ታጣቂዎች ሬሳ የቻለውን ሁሉ ጭኖ በመሸሹና የመንግሥት ኃይል ወደ ትግራይ ሲገባ መንግሥት በትግራይ ጅምላ ጭፍጨፋ ፈፀመ የሚል በአስከሬን የመነገድ እቅድን እንዳሰበ ስለተደረሰበት ነው ብለዋል፡፡ ከእውነት የራቁ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የሽብር ቡድኑን ክስ መነሻ በማድረግ የተለያዩ ወሳኔ ለማሳለፍ እንደሚሰሩ ይታወቃልም ሲሉ አክለዋል፡፡

መንግሥት የአገሪቱን የግዛት አንድነት የመጠበቅ ሙሉ ኃላፊነቱን ለመወጣት በየትኛውም ጊዜ ወደ ትግራይ ክልል እየገባ እርምጃ መውሰድ እንደሚችል የሚታመን መሆኑም 3ኛው ምክንያት ተብሏል፡፡

መንግሥት አሁን ላይ ምንም የማድረግ አቅም የሌለውን ትሕነግ መልሶ እንዳይነሳ ለማድረግ የሚያስችሉ የተጠኑ እርምጃዎችን በየትኛውም ስፍራ እየገባ ይፈፅማል ተብሏል፡፡

ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የአሸባሪውን ትሕነግ ቡድንን ጠራርጎ በማስወጣትና እጁን እንዲሰጥ በማድረግ ስኬታማ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ሚኒስትሩ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በሸባሪው ሸኔ የሚደርሱ ችግሮችን እንዲሁም በምዕራብ አማራ አካባቢዎች የሚወስዳቸው የተጠኑ እርምጃዎች ይቀጥላል፤ ቀጣይ አቅጣጫዎችንም ያሳውቃል ብለዋል፡፡