የወገን ጦር በተለያዩ ግንባሮች ድልን በመቀናጀት ወደ ፊት እየገሰገሰ መሆኑን መንግስት አስታወቀ

ኅዳር 22/2014 (ዋልታ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ዘመቻ ለኅብረብሔራዊ አንድነት በአንጸባራቂ ድሎች መቀጠሉን መንግስት አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሳወቁት የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ በጥምረት በወሰዱት እርምጃ የአርቢት፣ አቀት፣ ዳቦና ጋሸና ከተሞችን ከወራሪው ኃይል ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጥተው በወገን ጦር ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በዚህ ግንባር በርካታ የነፍስ ወከፍ እና የቡድን መሳሪያዎች መማረካቸውም ተጠቁሟል፡፡
በዚህም የአሸባሪው ቡድን የጠላት ጦር የዘረፋቸውን ንብረቶችና ራሱን ጭምር ይዞ መውጣት የሚችልበት እድል ሙሉ በሙሉ ዝግ ሆኖበታል ብለዋል፡፡
የወገን ጦር ጋሸናና አካባቢውን ከመቆጣጠር አልፎ በአሁኑ ሰዓት ወደ ላሊበላ፣ ወልዲያ እና ወገልጤና አቅጣጫ ወደፊት እየገሰገሰ ነው ብለዋል፡፡
በወረኢሉ ግንባር ደግሞ የጃማዶጎሎ፣ ወረኢሉ፣ ገነቴ እና ፊንጮፍቱ ከተሞችም ሙሉ በሙሉ ከወራሪው ኃይል ነጻ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
በሸዋ ግንባርም ተመሳሳይ ድል የተመዘገበ ሲሆን የመዘዞ፣ ሞላሌ፣ ሸዋሮቢት እና አካባቢው እንዲሁም ራሳና አካባቢው በወገን ጦር ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በምስራቅ ግንባር ከዚህ ቀደም ከወራሪው ኃይል ሙሉ በሙሉ ነጻ በወጡት የጭፍራ፣ አሳጊታ፣ ቡርቃ፣ ዋኢማ፣ ጭፍቱ፣ ድሬሮቃ፣ አለሌ ሱሉላ አካባቢዎች አሸባሪ ቡድኑን የመልቀሙ ስራ ተጠናቅቆ የነበረውን አስተዳደር መልሶ የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑንም መንግስት አስታውቀዋል፡፡
በነስረዲን ኑሩ