የወጪና የገቢ ንግድ ለማሳለጥ የተለያዩ የወደብ አገልግሎት አማራጮችን ለመጠቀም እየተሰራ ነው ተባለ

ሰኔ 1/2014 (ዋልታ) የሀገሪቱን የወጪና የገቢ ንግድ ለማሳለጥ የተለያዩ የወደብ አገልግሎት አማራጮችን ለመጠቀም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ገለጸ።

የብረትና ከሰል ምርቶች በታጁራ ወደብ በኩል ወደ ሀገር እንዲገቡ መደረጉም በጅቡቲ ወደብ ላይ የነበረውን መጨናነቅ እንደቀነሰው ተገልጿል።

ለአንድ ሀገር የተሻለ የሎጅስቲክ አፈፃፀም የወደብ አማራጮችን መጠቀም በመሠረታዊነት የሚታይና የወጪና ገቢ ንግዱን የሚያሳልጥ ሲሆን ኢትዮጵያ በሎጅስቲክስ ያላትን ዝቅተኛ የሎጅስቲክስ ደረጃ ለማሻሻል በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተተገበሩ ነው።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ያብባል አዲስ የሎጂስቲክ አፈጻጸምን ለማሻሻል በአማራጭ የወደብ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት አድርጓል ብለዋል።

አማራጭ ወደቦችን መጠቀም በወደቦች የሚኖረው መጨናነቅ በመቀነስ የአንድ ወደብ ጥገኝነትም እንዳይኖር ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል ነው ያሉት።

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሲጠቀም ከነበረው የጅቡቲ ወደብ ጎን ለጎን የታጁራ፣ የበርበራና የሞምባሳ ወደቦችን መጠቀም መጀመሩን ገልጸዋል።

የወደብ አማራጮችን መጠቀም በጅቡቲ ወደብ ላይ የነበረውን የእቃ ክምችት በማቃለልና የሎጂስቲክ ሥርዓቱን በመሳለጥ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ነው ያስረዱት።

የብረትና ከሰል ምርቶች በታጁራ ወደብ እንዲመጡ መደረጉም በጅቡቲ ወደብ ላይ የነበረውን መጨናነቅ እንደቀነስም ጠቁመዋል።

በዚህም በኮሪደሩ መነቃቃት የፈጠረበትና የኮሪደሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻሎችን እያሳየ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በታጁራ አማራጭ ወደቡ መጠቀም መቻሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በተጓዳኝም በጋራ ወደቦችን በማልማት ከጎረቤት አገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በ10 ዓመት መሪ እቅድ የአገሪቱን ገቢና ወጪ ጭነት አሁን ካለበት 17 ነጥብ 732 ሚሊዮን ቶን ወደ 30 ነጥብ 41 ሚሊዮን ቶን ከፍ ለማድረግ ታቅዷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሎጂስቲክ አፈጻጸም ደረጃ አሁን ካለበት 126ኛ ደረጃ ወደ 40 ለማድረስም እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።