የዋግኸምራን ዞን መልሶ ለማቋቋም መንግስት በትኩረት እየሠራ መሆኑ ተገለጸ

ነሐሴ 16/2014 (ዋልታ) የፌዴራል መንግሥት የዋግኸምራን ዞን የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰቆጣ ከተማ እየተከበረ በሚገኘው የሻደይ በዓል ላይ በመገኘት ነው ይሄንን መልዕክት ያስተላለፉት።

በዞኑ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለማቋቋም ግንባታዎች እንደሚካሄዱ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በዋግኸምራ ማህበረሰብና አካባቢው ላይ የህይወት፣ የአካልና የንብረት ውድመት ማድረሱን በማስታወስ ችግሩን ለመከላከል ህዝቡ ከመከላከያ ሰታዊት፣ ከልዩ ኃይሉና ሌሎችም የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ለተጫወቱት ሚና ምስጋና አቅርበዋል።

ሕወሃት ታላቋን ሀገር በማሳነስ ላይ ተጠምዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

መንግሥት አሁንም ከሕወሃት ጋር በሠላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲመጣ በአፍሪካ ህብረት በኩል እቅዱን ይፋ አድርጓል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁንና የሕወሃት ቡድን የጦርነት ነጋሪት ጉሰማውን ቀጥሏል ብለዋል።

በመሆኑም የሠላም ፀር በሆነው ሕወሃት ሊቃጣ ከሚችል ዳግም ትንኮሳ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሁም መላው የዓለም ማህበረሰብ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢብኮ ዘግቧል፡፡