የውሃ ትራንስፖርትን ማስፋፋት እና ማዘመን በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል – ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ


ሐምሌ 05/2013 (ዋልታ) – የውሃ ትራንስፖርትን ማስፋፋት እና የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ልዩ ትኩረት ተሰጠው መሆኑን የትራነሰፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትሯን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራር አካላት በጋምቤላ ክልል በባሮ ወንዝ ላይ የሚገኘውን የቀድሞ የጀልባ ማቆሚያ ግንባታንና የጋምቤላ ከተማ መናሃሪያን ጎብኝተዋል።
በሚኒስትሯ የተመራው ቡድን ጋምቤላ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጅሉን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ሚኒስትሯ በባሮ ወንዝ ላይ የሚገኘውን የቀድሞ የጄልባ ማቆሚያ ግንባታና የጋምቤላ ከተማ መናሃሪያን የጎበኙ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥ በቅድመ ግንባታ፣ በግንባታና በጥገና ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም እና ቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ መክረዋል፡፡
በቀጣይ 10 ዓመት የትራንስፖርት ዘርፍ መሪ የልማት ዕቅድ የውሃ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት እና ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ መናሃሪያዎችን በመገንባት የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በትኩረት እንደሚሠራ ሚኒስትሯ በጉብኝታቸው ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን እናልብስ በሚል የተጀመረውን የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ በማስቀጠል በጋምቤላ ክልል ችግኞችን በመትከልም አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ መርኃግብር መካሄዱን ከሚንስቴሩ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡