የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ግንቦት 13/2014 (ዋልታ) በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚታየውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት ‘’ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች’’ በሚል መሪ ቃል በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በድሬዳዋ ከተማ የተካሄደ ሲሆን ከኃይለስላሴ እስከ ብልፅግና የስልጣን ዘመን የተከናወኑ አበይት ኩነቶችን የሚያስቃኝ የፎቶ አውደ ርዕይም ለእይታ ቀርቧል፡፡

በውይይቱ ላይም የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አልበል የኢንቨስትመንት ዘርፉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚታየውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ምርታማነትን ማሳደግ እና ኤክስፖርት መጠን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ታምርት’’ ንቅናቄ በተከናወኑ ተግባራትም ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግና በተለይም የአመራሩ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ድሬዳዋ ለጅቡቲ ወደብ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ ሁሉንም የመሰረተ ልማት አውታሮች የተሟሉላትና የደረቅ ወደብ ባለቤት መሆኗ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ተመራጭነቷን ያጎላዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በአስተዳደሩ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እንዳሉት መንግሥት የግል ዘርፉን ለመደገፍ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ባለፉት ዓመታት የዘርፉን ፋይናንስ አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል፡፡

እንደ ሀገር የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከኢንቨስትመንት ዘርፉ ባሻገር በሁሉም ዘርፍ መረባረብ እና የሀገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

መንግሥት የግሉ ዘርፍን ለማበረታታት እያደረጋቸው ያሉ ድጋፎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት አመራሩ ከምንዛሬ እጥረት ችግር እንዲቀረፍ እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲተካ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

እንዲሁም አመራሩ ከባለሃብቶች ጋር በመቀናጀትና በመተባበር ዘርፉ ለሀገር ብልፅግና እያደረገ የሚገኘውን አስተዋፅኦ እንዲጎለብት ማስቻል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት የሚካሄደው ስለ ኢትዮጵያ የተሰኘው የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ እና  ‘’ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች’’ በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የፓናል ውይይትም በቀሪ 9 ክልሎች እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከድሬዳዋ)