የካቲት 30/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አዲሷን የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲን ትናንት በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል፡፡
ተወያዮቹ የሁለቱን አገራት የረጅም ጊዜ ወዳጅነት በማድነቅ፤ በተለይም በትምህርት፣ በጤና እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ ያለው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተስማምተዋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ካሉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ በአሜሪካ ትኩረት የሚሰጣት አገር መሆኗን አምባሳደሯ ጠቅሰው፣ በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ሁለቱ አገራት መተባበር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ ደመቀ በበኩላቸው፣ መንግሰት በትግራይ ክልል አስገዳጅ ሁኔታ ስለነበረ እና ሰላማዊ አማራጮች በህወሓት ቡድን ተቀባይነት በማጣታቸው ተገዶ ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ መግባቱን አስረድተዋል፡፡
ከዘመቻው በኃላ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ እና ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶች እና ሚድያዎች ያለ ገደብ እንዲቀሳቀሱ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አቶ ደመቀ ለአምባሳደሯ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ እስካሁን ለ3.8 ሚሊዮን ሰዎች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች መሰራጨታቸውን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ድጋፍ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው በመንግስት መሸፈኑን ጠቁመው፤ ዓለም አቀፍ ማህበረስብ ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡