የውጭ ጣልቃ ገብነት በመጠኑ እየቀነሰ መምጣቱን መንግስት አስታወቀ

ከበደ ደሲሳ

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) የአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ጣልቃ ገብነት እና መገናኛ ብዙኃን ሐሰተኛ ዘገባዎች እየቀነሱ መምጣታቸውን መንግስት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ ለጋዜጠኘች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ባለፉት ጥቂት ወራት የኅልውና ዘመቻውን በተሳሳተ አቅጣጫ በመውሰድ በዲፕሎማሲ ከፍተኛ ጫና እንደነበርና አሁን ላይ የአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ጣልቃ ገብነት እና መገናኛ ብዙኃን ሐሰጠኛ ዘገባዎች እየቀነሰ መጥቷል።

በያዝነው ሳምንት በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የቻይና አፍሪካ ትብብር ጉባኤ በቻይና የቀረበው  ግሪን ላይት የተሰኘው የልማት አቅጣጫም አፍሪካውያን የግብርና ምርቶቻቸውን ወደ ቻይና እንዲልኩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በፎረሙ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘውን የኅልውና ዘመቻ ለአፍሪካ ወዳጆች ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ታላቅ እምርታ መሆኑ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው አንዳንድ ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ በሐሰት መረጃ በሚያሸብሩበት ወቅት የሚኒስትሩ ጉብኝት በጎ ገፅታን የገነባ እንደነበር አመልክተዋል።

በሳምንቱ ውስጥ #በቃ #Nomore ዓለም ዐቀፍ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ የቀጠለበት ከመሆኑም ባሻገር በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት እንደነበርም አስታውሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባቀረበው ጥሪ መሰረት በቀጣይ በሚከበሩ አገራዊ በዓላት ላይ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ እንዲሆኑም መንግስት ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያ ሰላሟ የተረጋገጠ እና ልማቷ የተፋጠነ አገር መሆኗን ለዓለም ማሳየት ይገባናል ሲሉም አክለዋል።

የውጭ ሚዲያዎች እና አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት የኢትዮጵያን መንግስት በሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም በሐሰት የከሰሱ መሆናቸው ተገልፆ   የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን በማጣራት ሐሰትነቱን ማጋለጡንም አንስተዋል፡፡

በቁምነገር አሕመድ