የዓለም ምግብ ፕሮግራም መንግሥት ግብርናውን ለማሳደግ እያደረገ ያለው ጥረት አደነቀ

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) መንግሥት በግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ፡፡
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ክሎድ ጅብዳር ጋር በመሰረተ ልማት ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በተለይም የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻልና የግብርና ልማት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ የክልሉ መንግሥት የክልሉ ሕዝብ ከውጪ የሚገቡ ምግብ ጥገኝነት በመላቀቅና ማኅበረሰቡ በሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት እንዲያተኩርና የሀገር ውስጥ ግብርና ምርቶች የማሳደግ ባህል እንዲዳብር በታቀዱ ስትራቴጂዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በሶማሌ ክልል በተደጋጋሚ ለሚከሰተው ድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎች በዘላቂነት ለመቋቋም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮና የመስኖ ልማት ሥራዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ክሎድ ጅብዳር በበኩላቸው መንግሥት በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ ያለውን ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግሥትም ማኅበረሰቡን ወደ ግብርና ሥራዎች እንዲያመራ የታለመው ዕቅድ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መናገራቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።