የዓለም ምግብ ፕሮግራም የትምህርት ቤት ምገባን እንዲደግፍ ተጠየቀ

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአዲስ መልክ የተጀመረውን የትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም በሁሉም ክልሎች እንዲስፋፋ ድጋፍ እንዲያደርግ የትምህርት ሚኒስቴር ጠየቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በኢትዮጵያ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ክላውዴ ጂቢዳር ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት በትምህርት ዘርፉ የትምህርት ጥራት መሻሻያ ሪፎርሞች መጀመራቸውን እና በትምህርት ቤት ምገባ ዙሪያም እየተሰሩ ስላሉ ሥራዎች ገልጸዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በአዲስ መልክ የተጀመረውን የትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም በሁሉም ክልሎች እንዲስፋፋ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተርም ተቋሙ ከትምህርት ቤት ምገባ በተጨማሪ በርካታ የምግብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው ለውጤታማነቱ የመንግሥት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በትምህርት ዘርፍ የተጀመረው ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቃቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

የትምህርት ቤት ምገባ በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ ክልሎች እየተተገበረ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW