የዓለም ባንክ ለጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት የ14.6 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አጸደቀ

ጥር 27/2014 (ዋልታ) የዓለም ባንክ አካል የሆነው ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ለቀጣይ 18 ወራት በጥራት ቁጥጥር ሥራ ላይ ለተሰማሩ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት የ14 ነጥብ 6 ሚሊዮን አሜሪካን ዶላር በጀት አጽድቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ላለፉት አምስት ዓመታት የጥራት መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ማሻሻል ዓላማ አድርጎ በመሥራት በአገልግሎት ሰጪ እና ተቀባይ አካላት መካከል ሚዛናዊ አሰራርን ለመፍጠር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን ጨምሮ በግሉ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች በርካታ የአቅም ግንባታ እና የመሰረተ ልማት ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱን የፕሮጀክት ጽ/ቤት አስተባባሪ ወንዶሰን ፍስሃ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በተለይም የምግብ፣ የጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ዘርፎች ምርትና አገልግሎት ጥራት ያለው እንዲሆን ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ይህንንም እውን በማድረግ በኩል በዘርፎቹ የሚስተዋሉ የምርት ጥራት እና አገልግሎትን ከነበረበት ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው እንቅስቀሴም የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል እና ዓለም ዐቀፍ እውቅና እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመለክተዋል፡፡

እ.ኤ.አ ከ2017 ሐምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው ይህ ፕሮጀክት ለጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት አስፈላጊው የአቅም ግንባታ እና የመሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ 38 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለቀጣይ አንድ ዓመት እንደተራዘመ እና የጸደቀው የ14 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማቱ እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም ድረስ ለሚያከናውኑት የሥራ እንቅስቃሴ የሚውል መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://www.facebook.com/waltainfo

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!