መጋቢት 25/2013 (ዋልታ) – የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሪፎርም መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
የባንኩ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ምክትል ፕሬዘዳንት ሃፌዝ ሃኔም እንደገለፁት፣ ባንኩ ሀገሪቱ ተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ ክትባት እንድታገኝ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባንኩ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመደገፍ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ሁለቱ አካላት በበይነ መረብ ባካሄዱት ስብሰባ የገንዘብ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ስላሉበት ሁኔታ ማብራርያ ሰጥተዋል።
አቶ አህመድ ሽዴ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የውጭ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግና ንግድን በቀላሉ ለመከወን የሚያስችል ምቹ መደላድል ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ የህግ መሻሻያዎችንም ጠቅሰዋል።
በመንግስት የሚተዳደሩ ኩባንያዎች ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው አሰራር እንዲመሩ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
የትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትም ማብራርያ ሰጥተዋል።
ባንኩ እነዚህን ተግባራት ጨምሮ የኮቪድ-19 ክትባት ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ላሳየው ቁርጠኝነትም ምስጋና ማቅረባቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።