የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ አጋርነቱን እንደሚቀጥል ገለጸ

መጋቢት 13/2014 (ዋልታ) የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ በልማት አጋርነቱ እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡
የዓለም ባንክ የአፍሪካ ዳይሬክትር ታውፊላ ንያማድዛቦ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ደ/ር) እና ከጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ጋር ባንኩ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍ ስለሚጠናከርበትና በባንኩ ድጋፍ እየተከናወኑ ባሉና ወደፊት በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በምጣኔ ሀብት ማሻሻያው ስለተሰሩ ሥራዎች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለማዘመንና ለማሻሻል ስለተደረጉ ጥረቶችም መክረዋል፡፡
የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስክ መሰማራት እንዲችሉ እየተሰጡ ስላሉ ድጋፎች፣ የግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይም በመስኖ የስንዴ ልማት ለማሳደግ እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች ውይይት ተደርጓል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ስለሚደረጉ ጥረቶች፣ በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች እየተሰጠ ስላለው ሰብኣዊ አርዳታ፣ በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ የመገንባት ሂደት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ስለመቋቋሙ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ የልማት አጋር መሆኑን አመልክተው ባንኩ ለመሰረተ ልማቶች ግንባታና ለመሰረታዊ አገልግሎቶች መስፋፋት ለሚሰጠው ድጋፍና ምጣኔ ሀብታዊ ትብብር ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በበኩላቸው የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ በግጭት፣ በድርቀና በኮቪድ 19 ጉዳት ውስጥ አልፋ አሁንም በልማት ጎዳና ለመራመድ የምታደርገውን ጥረት መገንዘባቸውን አመልክተው የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የዓለም ባንክ በልማት አጋርነቱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍ አገሪቱ በጦርነት፣ በድርቅና በኮቪድ የደረሰባትን ጉዳት ለመቋቋም የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው ከዓለም ዐቀፉ የልማት ድርጅት የሚገኘው ውጭ ሀብት የትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ መጠጥ ውሀና መንገድ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋትና ኢትዮጵያ የነደፈችውን የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ እውን ለማድርግ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በዛሬው እለት ከገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴና ከሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በየተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡