የዓለም ዋንጫ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለእይታ ሊመጣ ነው

ሚያዝያ 26/2014 (ዋልታ) የዓለም ዋንጫ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለእይታ የሚመጣ ሲሆን የሁለት ቀናት ቆይታ እንደሚኖረው ተገለፀ፡፡

የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ አስቀድሞ የዓለም ዋንጫ ለእይታ ከሚቀርቡባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ነች።

ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የዓለም ዋንጫ ተመሳስሎ የተሠራ ሳይሆን ትክክለኛው ዋንጫ በመሆኑ ይህ ለእግር ኳስ አፍቃሪያን ትልቅ እድል መሆኑን የዝግጅቱ አስተባባሪ ዳረን ዊልሰን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ባናልፍም አገሪቱ ይህን እድል ማግኘቷ እግር ኳስ ላይ ጠንክረን ሰርተን ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት እንድንሸጋገር የሚያሳስብ ነው ብለዋል፡፡

ከዓለም ዋንጫው ጋር እውቁ ፈረንሳዊ ዴቪድ ትሪዝጌት አብሮ የሚመጣ ሲሆን ግንቦት 17 በመስቀል አደባባይ እና በተመረጡ ቦታዎች ለእግር ኳስ አፍቃሪዎች ለእይታ እንደሚቀርብ ተነግሯል፡፡

በትዝታ ወንድሙ